በ2016 በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ከወጡ አዋጆች አንዱ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥር እና አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1320 መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህ አዋጅ ዋነኛ አላማው የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋ ከጊዜ ወደጊዜ እየናረ እና በዜጎች ኑሮ ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረ በመሆኑ እና የመኖሪያ ቤት አንገብጋቢ እና መሰረታዊ የመብት ጉዳይ እንደመሆኑ መንግስት የመኖሪያ ቤትን አቅርቦት ለማሟላት ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን ይህን አዋጅ ማውጣት ማስፈለጉ እንደሆነ በህጉ ተመልክቷል፡፡
ይህ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥር እና አስተዳደር ግልጽነት ፣ ተጠያቂነት ያለው እና የአከራዮችን እና ተከራዮችን ጥቅም እና መሰረታዊ መብቶች ሚዛን በጠበቀ መል ለማስተናገድ የሚያስችል የህግ ማእቀፍ አስፈላጊ በመሆኑ በፓርላማው ጸድቆ ወጥቷል፡፡ ,
1. የአዋጁ ተፈጻሚነት፡-
1.1. ይህ አዋጅ ተጠሪነታቸው ለክልል በሆኑ ከተሞች ፣ በአዲስ አበባ እና በድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ላይ በሚፈጸም የመኖሪያ ቤት ኪራይ ላይ ተፈጻሚ ነው፡፡
1.2. በሆቴል ሪዞርት የእንግዳ ማረፊያ ለመኖሪያ የሚከራዩ ቤቶችን አስመልክቶ አዋጁ ተፈጻሚነት የለውም፡፡ (አንቀጽ 3)
2. የመኖሪያ ቤት ኪራይ ውል ዘመን፡-
2.1. የመኖሪያ ቤት ኪራይ የውል ዘመን ከ2 አመት ሊያንስ አይችልም፡፡ (አንቀጽ 6)
2.2. የቤት ኪራይ ውል ዘመን ሳይጠናቀቅ ተከራይን ከቤት ማስወጣት ወይም በአዋጁ ከተመለከተው ውጪ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ አይቻልም፡፡
2.3. ይህ አዋጅ ከመውታቱ በፊት በጽሁፍ የተደረገ የመኖሪየ ቤት ኪራይ ውል ዘመን በውሉ ላይ የተቀመጠው ዘመን ይሆናል፡፡ ስለሆነም አዋጁ ከመውጣቱ በፊት በተደረገ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ውል ለ6 ወር ለ1 አመት ውል ዘመን የተደረገ ቢሆን ተከራይ ቤቱን ከ6 ወር ወይም 1 አመቱ ውል ዘመን ማብቂያ በኋላ ቤቱን ለመልቀቅ ይገደዳል፡፡ ቤቱን የመልቀቅ ፍላጎት ከሌለው ደሞ በአከራዩ በሚሰጠው የኪራይ ውል ማሻሻያ ዋጋ ጭመራ መሰረት በቤቱ ተከራይነቱ ሊቀጥል ይችላል ማለት ነው፡፡ ስለሆነም ከአዋጁ በፊት የተደረገ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ውል የ2 አመቱ ገደብ አይመለከተውም፡፡
2.4. የአንድ ቤት ባለቤትነት በውርስ ፣ በሽያጭ፣ በእዳ ፣ ወይም በሌላ በማናቸውም ህጋዊ ምክንያት ለሌላ ወገን ከተላለፈ የመኖሪያ ቤት ኪራ ውሉ ቤቱ ከተላለፈበት ጊዜ ጀምሮ ለተከራዩ በሚሰጥ የ6 ወር ማስጠንቀቂያ ይቋረጣል፡፡
ነገር ግን ቤቱ የተላለፈለት ገዢ ወይም ወራሽ ፈቃደኛ ከሆነ ተከራይ ቤቱን እንደተከራየው ሊቀጥል ይችላል፡፡
2.5. የቤቱ ባለቤትነት በስጦታ ከሆነ የተላለፈው የመኖሪያ ቤት ኪራይ ውል ዘመኑን አያቋርጥም፡፡ በስጦታ ቤቱን የተረከበው ሰው የቀድሞውን አከራይ ተክቶ በኪራይ ውሉ መሰረት የአከራይን መብቶችና ግዴታዎች ይሸከማል፡፡
3. የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋ፡-
3.1. የአንድ የሚከራይ ወይም የተከራየ ቤት የኪራይ ዋጋ ተደርጎ የሚወሰደው በአዋጁ መሰረት የተመዘገበው የኪራይ ውል ላይ ያለው የኪራይ ዋጋ ነው፡፡ (አንቀጽ 8)
3.2. ስለሆነም አከራይ ቤቱን ነባሩን ተከራይ አስወጥቶ ለአዲስ ተከራይ ቢያከራይም የማከራየ ዋጋ ተደርጎ የሚወሰደው በተመዘገበው ውል ላይ ያለው ዋጋ ነው፡፤
3.3. አከራይ ለነባር ተከራይ ወይም አዲስ ተከራይ በሚያከራየው ዋጋ ላይ ለውጥ ማድረግ የሚችለው የመኖሪያ ቤት ኪራይ ውልን እና ዋጋን እንዲቆጣጠር በክልል የሚሰየም አካል በአመት አንድ ጊዜ ነባራዊ የኢኮኖሚውን ሁኔታ እና ሌሎች አግባብነት ያላቸውን ጉዳዮች ከግምት በማስገባት ሊወስን የሚችለውን መኖሪያ ቤት ኪራይ ጭማሪ መሰረት በማድረግ ብቻ ነው፡፡ (አንቀጽ 8(4))
3.4. በተጨማሪም ከላይ በተራ ቁጥር 3.4 በተገለጸው መልኩ በተቆጣጣሪው አካል ውሳኔ መነሻነት የኪራይ ዋጋ የውል ዘመኑ 2 አመት ባላለቀ የቤት ኪራይ ውል ዋጋ ላይ ጭማሪ ሲያደርግ ያደረገውን የኪራይ ዋጋ ማሻሻያ ለተቆጣጣሪው አካል ማሳወቅ በጽኁፍ ማሳወቅ አለበት፡፡
በአጠቃላይ ከላይ በተጠቀሰው አዋጅ የመኖሪያ ቤት አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ መሰረት አንድ የመኖሪያ ቤት አከራይ ቤቱን ሲያከራይ የሚያከራይበት የውል ዘመን እንዲሁም የኪራይ ዋጋ ለተዋዋይ ወገኖች ያልተተወ ይልቁንም በህግ የሚገዛ ነው፡፡
አንድን የመኖሪያ ቤት ለማከራየት የሚቻለው ዝቅተኛ የውል ዘመን 2 አመት ሲሆን ከ2 አመት በፊት የኪራይ ዋጋን ማሻሻልም በአዋጁ ተከልክሏል፡፡ በልዩ ሁኔታ ተቆጣጣሪው አካል ፈቃድ ብቻ የኪራይ ውሉ ከዋጋ አንጻር ሊሻሻል ይችላል፡፡
📞 የህግ እገዛ ከፈለጉ
Fiker Getachew & Associates Law Office
☎️ +251911992719